Tuesday, February 13, 2018

Tuesday, September 7, 2010

ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ቀን በደመቀ ሁኔታ ተከበረ።

ይገርማል ጊዜ ሲገሰግስ። የኢትዮጵያ ቀን ከተጀመረ ዘጠኝ አመታት አለፉት። ከተጀመረ የማይቀጥል ነገር የለምና ከዓመት ወደዓመት ኢትዮጵያውያን ባህል ብለን ይዘነው በናፍቆት የምንጠባበቀው ዓመት-በዓል ሆኗል። ባለፉት ቅዳሜና እሁድ ሴፕቴምበር 4 ና 5 ቀን 2010 (በአውሮፓውያን አቆጣጠር) ዘጠነኛው የኢትዮጵያ ቀን ለሁለት ቀናት ተከብሮ ውሏል። የኢትዮጵያ ቀን በኢትዮጵያውያን የጋራ መረዳጃ ማሕበር፣ በዳላስና ፎርት ወርዝ፣ ክዛሬ 26 ዓመት በፊት በ1984 ዓ.ም. የተመሠረተ ከታክስ ነጻ የሆነ በቴክሳስ ክፍለ ሀገር በሕግ የተመዘገበ ድርጅት ሲሆን ከ2002 ጀምሮ ሳያቋርጥ በየዓመቱ ይከበራል።

ያሁኑ ዝግጅት ኦክሊፍ በሚባለው የዳላስ ደቡብ የከተማ ክልል በሚገኘው ስካይላይን ራንች በሚባለው ሥፍራ ሲሆን ይህ ሶስተኛው ዝግጀት ይመስለኛል። ሁለተኛውና ሌላ አንድ ዓመት በዚሁ ሥፍራ ነበር የተደረገው። ቦታው አመቺና ሰፋ ያለ ከከተማው ግርግር ወጣ ያለ ቢሆንም አብዛኛው የህብረቴሰባችን ክፍል የሚኖረው በሰሜንና ሰሜን ምሥራቅ የሜትሮፕሌክሱ ክፍል በመሆኑ በብዙዎቹ የርቀትን ስሜት አስከትሏል። ከመንገዱ መራቅ ይልቅ፣ ከዳላስ መሀል ከተማ ወይም ዳውንታውን በስተደቡብ አልፎ መሄድ ያልተለመደ መሆኑ ለዚህ የባይተዋርነት ስሜት አስተዋጽኦ ያለው ይመስላል።

ይሁን እንጂ የተሳታፊዎቹ ቁጥር ቀላል አልነበረም። እንደተለመደው ነጋዴዎች (ቬንደሮች) እንደሌላው ጊዜ ባይበዙም በመጠኑ ነበሩ፦ በተለይም ምግብና ለስላሳ መጠጦችን አንዲሁም አንዳንድ ቁሳቁሶችንና አገልግሎቶቻቸውን የሚያስተዋውቁ ነበሩ። የንግድ ድርጅቶች ብቻ ሳይሆኑ አትራፊ ያልሆኑ የባለሙያተኞች ማሕበራት የሀይማኖት ድርጅቶችንም ጨምሮ ይታዩ ነበር።

የምሽቱ ድምጻዊ ዝነኛው የአገር ባሕል ድምጻዊ ተጫዋች ይሁኔ በላይ ሲሆን፣ በልዩ ልዩ የኢትዮጵያ ቋንቋዎች የአገራችንን ሙዚቃዎች በመጫወት በሁለቱም ምሽቶች ከትንሽ እስከ ትልቅ ከመድረኩ ሳይለይ በስሜት እንዲጨፍር አድርጓል።

የሬጌ ባለሙያ የሆነው ጃማይካዊው ድምጻዊም በተለይ ወጣቶቹንና ሕጻናቱን ሲያስደስት መንቀሳቀስ እስከሚያቅተው ድረስ ከአሰር አመት እድሜ ባነሱ ህጻናት ጭምር ተከቦ ያነገተውን የኤለክትርክ ጊታሩን እንዲጠነቆሉለትና እንዲነዘሩለት ፈቅዶላቸው እንዲፈነጥዙ ሲያደርግ አምሽቷል።

የኢትዮጵያ የጋራ መረዳጃ ማሕበሩ በርከት ያሉ በጎ ፈቃደኞች አሰማርቶ ስለነበር በማስተናገድ፣ ጥያቄዎችን በመመለስ እንዲሁም ልዩ ልዩ የስራ ዘርፎች ላይ ተሰማርቶ በዓሉን ለማድመቅ በመቻላቸው ስኬታማነቱ እንዲቀላጠፍ ረድቷል።

ከሁሉም በላይ አዲስ የተመሰረተው ወጣቶች ማሕበር (ከአስራ ሶስት እስከ ሰላሳ ዓመት እድሜ) ልዩ ልዩ ተስፋ የሚሰጡ ንግግሮችን ከማድረጋቸውም ሌላ የኢትዮጵያ ብሔረሰብ የባህል ትእይንቶችን በማሳየት ሁለቱንም ቀናት ታዳሚዎቹን በኪነት ውዝዋዜ ሲያስደስቱ አምሽተዋል።

የቦርዱ አባላት በመቀባበል ወቅቱን እየጠበቁ ማስታወቂያዎችንና ማሳሰቢያዎችን በማቅረብ ልዩ ልዩ የመረዳጃ ማሕበሩ ኮሚቴዎች የስራቸውን ድርሻ ምን ላይ እንደደረሰ መግለጫ እንዲሰጡ በማድረግ የእንግዶቹን ስሜት ሲቀሰቅሱና ሲያስደስቱ ታይተዋል።

የባስኬት ቦልና የቮሊቦል የመሳሰሉ የስፖርት ዝግጅቶች እንዲሁም የጠረጴዛ ኳስ ጨዋታዎች መኖራቸው ለበዓሉ ልዩ ድምቀት ከመስጠቱም አልፎ ወጣቶቹ በነዚህ እንቅስቃሴዎች ሲሳተፉ ማዬትና ድጋፎችን መስጠት በተለይ ወላጆች ለሆኑት አንድ ተቀዳሚና ዋና ክንዋኔ ነበር።

የማቀነባበሩ ጉዳይ ላይ ማሻሻል የሚችሉ ብዙ ነገሮች ቢኖሩም የሕዝቡን ስሜት በአሉታዊ መንገድ ስላላወከ ድክመቱ እንደዘበት ችላ ተብሎ ቢታለፍ ክፉ አይደለም። ከዚህም ትምሕርት ወስዶ ለሚቀጥሉት ዝግጅቶች ማሻሻያ ማድረግ ይቻላል የሚል ግምት አለ።

የእለቱ ዋና ተግባርና ከሁሉም በላይ ለወደፊት መሠረት ጥሎ የሚያልፈው ጉዳይ ለማሕበረሰባችን ቋሚ የሆነ የመናኸሪያ ቦታ ለመግዛት የሚያስችል ገንዘብ ማሰባሰቢያ ወቅትና ቀደም ብለው ለማሕበረሰቡ ላገለገሉት ግለሰቦች የተደረጉት የሽልማት ዝግጅቶች ናቸው። ያሁኑን ልዩ የሚያደርገው በኮሚቴው ውስጥ አባል ሆነው የሚሰሩት ግለሰቦች ከልብ የመነጨ አስተዋጽኦና ከወትሮው "ራስን ከመሸጥና ከማስተዋወቅ" ያለፈ የሚመስል አቀራረብ ታዳሚው ላይ ያሳረፈው የሀቀኝነት ስሜት ነው። ገንዘብ ለማዋጣት የነበረው ሞራልና ስሜት ከሌላው ጊዜ የበለጠ በመሆኑ ባልሳሳት ከኮሚቴው አንዱ “እስከ ሰማንያ ሺህ ድረስ ቃል-ሳይገባልን አይቀርም” ብለዋል። ይህ እውነት ከሆነ በውነቱ የሚደነቅ ሥራ ነው።

ሌላው ልዩ ገጽታ ደግሞ ከተለመደው የርስ በርስ መሸላለም ውጭ ያልተገመቱና ከወተሮው ወጣ ብለው ማሕበረሰቡን ሰፋ አድርጎ ለማቀፍ በሚል ስሜት ይመስላል ቦርዱ ጥቃቅን ቅራኔዎችና ቅሬታዎች ሳያውኩት ማሕበረሰቡን ያለአድልዎ ለማስተናገድ ዝግጁ መሆኑን ያመላክታል። የማሕበሩ መስራቾች፣ የስፖርት ፌደረሽኑ መስራቾች ከሆኑት አንዱ፣ እንዲሁም የሴቶች ማሕበር መስራችና የኮሚኒቲው የራዲዮ ዝግጀት መስራች የሆነው ግለሰብ የመሳሰሉት መሸለማቸውና እንዲታወቁ መደረጋቸው ትልቅ የማሕበራዊ እድገት መኖሩንና ክጠባብ አስተሳሰብ መላቀቃችንን አመላካች ነው።